ጽዋዕ ማለት በቁሙ

ጽዋ

ጽዋዕ ማለት በቁሙ ኩባያ’ዋንጫ’የመጠጥ መሣሪያ የሚል ትርጉም አለው፡፡ በሌላም በኩል በጽዋ ተቀድቶ የሚሰጥም መጠጥ ጽዋ ይባላል፡፡ ማኅበር ማለት ደግሞ‹‹ኀብረ›› አንድ ሆነ ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ነው፡፡ በአንድ ላይም ጽዋ ማኅበር ማለት በጽዋ ለመጠጣት የሚሰባሰቡ የምእመናን አንድነት ማለት ነው፡፡ ጽዋ ማኅበር ምእመናን በወር ወር ተራቸውን እየጠበቁ እየደገሱ የሚያበሉበት እንዲሁም ችግረኞችን የሚረዱበት ሥርዓት ነው፡፡ በጽዋ ማኅበር መሳተፍ በረከትን ያሰጣል (መዝ 3.8′ ምሳ10.7) እንዲሁም በማቴ 10.42 ላይ እንደተገለጸው ዋጋን አያጠፋም፡፡

ማኅበሩ በጌታችን’በእመቤታችን’በቅዱሳን መላእክት’በጻድቃንና በሰማዕታት ዕለት በቤተክርስቲያን ዙሪያ ወይም በምዕመናኑ ቤት የሚካሄድ ነው፡፡ ማኅበርተኖቹም ከእኅትና ከወንድምነት ባለፈ እርስ በእርሳቸው በጋብቻ መተሳሰር የለባቸውም፡፡ የአንድ ጽዋ ማኅበር አባላት ብዛት አሥራ ሁለት መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም በዓመት ውስጥ ያሉት ወራት አሥራ ሁለት በመሆናቸው ሁሉም አባል ተራው እንዲደርሰው ነው፡፡ ከአሥራ ሁለት በላይ ከሆኑ ግን ድርብ/ደባል/ በሚባለው አከፋፈል መሰረት በወር ውስጥ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ሆነው በመመደብ ተራቸውን እንዲያወጡ

ይደረጋል፡፡

የጽዋ ማኅበር አመሰራረት ትውፊታዊ ባህልን የተከተለ ነው፡፡ በዘመነ ሥጋዌ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች በአንድነት የፍቅር ማዕድ /አጋፔ/ ይመገቡ ነበር፡፡ ኋላም ቅዱሳን ሐዋርያት ከጌታ እርገት በኋላ ካመኑና ከተጠመቁ ክርስቲያኖች ጋር በአንድነት ኑሯቸውን እንዳደረጉ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ ሐዋ.ሥራ 2.44-47
በዘመነ ሰማዕታት ግን ይህ ሁኔታ በአብዛኞቹ   ክርስቲያኖች ተረስቶ ነበር፡፡ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ግን ይህ ትውፊት በአባቶታቻችን ጸሎት’ብርታት ባህሉ ወጉ ሥርዓቱ ሳይፋለስ ተጠብቆ ለትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ ቆይቷል፡፡ የቤተክርስቲያን ታሪክ እንደሚነግረን በኢትዮጲያ የመጀመሪያው የጽዋ ማኅበር መሥራች አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ሲሆኑ ወቅቱም በ330 ዓ.ም በአክሱም ነበር፡፡ የማሕበሩ ስም በመጀመሪያ ‹‹ማኅበረ ጽዮን›› ይባል የነበረ ሲሆን ቆይቶ ‹‹ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊ›› ተባለ በመጨረሻም ‹‹ጽዮን ማርያም›› በመባል ስሙ ሊለወጥ ችሏል፡፡ በ14ኛው መ/ክ/ዘ አፄ ዘርዓያዕቆብ ሕዝቡን በሃይማኖቱ የበለጠ ለማጽናት በማሰብ በቅዱሳንና በእመቤታችን ስም ማኅበር እንዲጠጣ ሕግ አወጡ፡፡ ቀጥሎም
በ16ኛው መ/ክ/ዘ ማኅበረ ሰላም መድኃኔዓለም የተባለ በአቡነ መብዓጽዮን የተቋቋመ ማኅበር እንደነበር የቤተክርስቲያን ታሪክ ይነግረናል፡፡